ሥውር ትስስሮችን በማጋለጥ፣ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ!

ግንዛቤ ማሻሻያ

ሥውር ትስስሮችን በማጋለጥ፣ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ!

****************

በሥውር ትስስሮች ከሚፈጸሙ የሙስና ወለድ ወንጀሎች መካከል በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ የማስመሰል ድርጊት አንዱ ነው። ይህ ወንጀል የሕገወጥ ሀብት ምንጭ በመደበቅ፣ የወንጀሉን አሻራ በማጥፋትና ሀብቱን ሕጋዊ በማስመሰል ያለ ተጠያቂነት ለመጠቀም የሚያስችል አደገኛ ወንጀል ነው።

የሙስና ፈጻሚዎች ከጉቦ፣ ከሕዝብ ሀብት ምዝበራ፣ ከሥልጣን አላግባብ አጠቃቀምና ከሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች የሚያገኙትን ጥቅም ምንጭ ለመደበቅና በነፃነት ለመጠቀም ሀብቱን በማሸሽ ሕጋዊ ለማስመሰል ይሞክራሉ። በዚህም ገንዘቡን በሐሰተኛ የንግድ ሥራዎች፣ በሌሎች ሰዎች ስም በሚመዘገቡ ንብረቶች፣ በሐሰተኛ ውሎችና በተደራራቢ የገንዘብ ዝውውሮች አማካኝነት ሕጋዊ ለማስመሰል ይጠቀማሉ።

በዚህ ሂደት የመጀመሪያውን ወንጀል ያቀናበሩ፣ ያመቻቹ፣ ምንጩን የደበቁና ከሀብቱ የሚጠቀሙ አካላት ይሳተፋሉ። ዓላማቸውም የወንጀሉን አሻራ ማጥፋትና ገቢውን ወደ ሕጋዊ ኢኮኖሚ ማስገባት ነው።

ይህ ወንጀል የሕዝብ ሀብትን ከልማት ያስቀራል፣ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ውድድርን ያዛባል፣ ሕገወጥ ሀብት እንዲከማች ያደርጋል፤ የተቋማትን ተዓማኒነትና የሕዝብን በሕግና በመንግሥት ላይ ያለውን እምነትም ያዳክማል።

በተጨማሪም፣ ወንጀለኞች ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጡና ሕገወጥ ጥቅማቸውን እንዲያስቀጥሉ ዕድል በመፍጠር የሙስናን ችግር ያባብሳል።

ይህንን ወንጀል ለመከላከል ተቋማት በቅንጅት መሥራት፣ የሀብትን ምንጭ፣ ባለቤትነትና የገንዘብ ዝውውር መከታተል፣ ማስረጃዎችን ማጠናከርና በወንጀል የተገኘ ሀብትን በሕግ ማስመለስ ይጠበቅባቸዋል። በወንጀሉ የተሳተፉና ያመቻቹ አካላትም ለሕግ ተጠያቂ መሆን አለባቸው።

ዜጎች አጠራጣሪ የሀብት መጠን መብዛት፣ ከገቢ ምንጭ ጋር የማይመጣጠን ንብረትንና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ሲያስተውሉ በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ በመደገፍ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት ይገባቸዋል።

ይህም ሕገወጥ ሀብትን ከምንጩ ለመከታተልና ወንጀለኞችን ለማስጠየቅ ያግዛል።

ሕገወጥ ጥቅምን አለመቀበል፣ የሕዝብ ሀብትን መጠበቅ፣ የሙስና ድርጊቶችን በማስረጃ ማጋለጥና ለተጠያቂነት መቆም የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው።

የሙስና ትግል ውጤታማ የሚሆነው ወንጀሉን የፈጸሙትን ብቻ ሳይሆን ያመቻቹትን፣ የደበቁትንና ከሕገወጥ ሀብቱ የተጠቀሙትንም ለሕግ ተጠያቂ ማድረግ ሲቻል ነው።

ስለሆነም፣ ተቋማት በቅንጅትና በተጠያቂነት መሥራት፣ ሕብረተሰቡም አጠራጣሪ ድርጊቶችን በመረጃና በማስረጃ በማጋለጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በጋራ ጥረት ሕገወጥ ሀብትን ማጋለጥ፣ ወንጀለኞችን ማስጠየቅና የሙስናን ሰንሰለት መበጠስ ይቻላል።

ሥውር ትስስሮችን በማጋለጥ፣ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ!

(Via: ፌ.ሥ.ፀ.ኮ)

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *