“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!!”አቶ ገመዳ ቡሊ (የሙስና ወንጀሎችና ብልሹ አሰራር መከላከል ዳይሬክተር)
*********************
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በጤናው ዘርፍ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ የአሰራር ሂደቶችን በዳሰሳ ጥናት ለይቷል፡፡ በዚህ ጥናት ለሌብነትና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ የአሰራር ሂደቶችን ማረቅ የሚያስችል ስልጠና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ለቢሮው አስተዳደር ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ረጋሳ ቢሮው በተቋሙ ውስጥ ለሌብነትና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ ጉድለቶችን መስመር ለማስያዝ ከክልሉ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በቀጣይነት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መልዕክት ያስተላለፉት በኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሎችና ብልሹ አሰራር መከላከል ዳይሬክተር አቶ ገመዳ ቡሊ በህክምናው ዘርፍ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚባለው፤ ሌብነትን አስቀድሞ መከላከል ሙስናና ብልሹ አሰራር የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችል አጽኖት ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ የሚስተዋለው ሌብነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የሚያደርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም ያሉት አቶ ገመዳ ዘርፉ ከፍተኛ በጀት የሚንቀሳቀስበት እና አላማውም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ማዳን በመሆኑ የሚያደርሰውን ጉዳት የተለየ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
በእነዚህና ሌሎች ወሳኝ ምክንያቶች በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሌሎች ተቋማት በተለዬ ሁኔታ በሥነ-ምግባር እንዲታነፁና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታማኝነት እና በቅንነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም ስልጠናውን በበጀት የደገፈውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ያመሰገኑት ዳይሬክተሩ መሰል የትብብር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል ቢችሉ ማህበረሰቡ በሙስናና ብልሹ አሰራር ከሚደርስበት እንግልትና መማረር በቀላሉ መታደግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
በዚህ ስልጠና የተሳተፉት የጤና ቢሮ የአስተዳደር ሰራተኞች (የማኔጅመንት አባላት) እና ባለድርሻ አካላት በጤናው ዘርፍ ከግዥ፣ ከሰራተኛ ቅጥርና ልማት ፣ ከጤና ተቋማት ግንባታ፣ ከበጀት አጠቃቀም እና ከገቢ አሰባበሰብ ጋር በተገናኘ ለሙስናና ብልሹ አሰራር አወንታዊ ሚና ያላቸው አሰራሮች መኖራቸውን ገልፀው፤ ችግሩ ብዙ ተዋናይ የሚስተዋሉበት በመሆኑ ይህንኑ ለመፍታት ቀጣይነት ያላቸውን ስራዎች ከኮሚሽኑ፣ ከሌሎች ተቋማትና ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል፡፡
