የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ሊተገበሩ እንደሚገባ ኮሚሽኑ አስታወቀ።

ወቅታዊ መረጃ
(አሶሳ ህዳር 14/2017 ዓ.ም፤ የቤጉክ የሥ/ፀረ – ሙስና ኮሚሽን) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በፕሮጀክቶች አፈጻፀም የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚመጡ ፕሮጀክቶች የመጡበትን አላማ እንዲያሳኩ ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ መሰል ፕሮጀክቶች ከሙስናና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ስለመንቀሳቀሳቸው በተለያዬ ደረጃ ክትትል እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ በክልሉ በስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ልማት ፕሮጀክት DRDIP አፈጻጸም ዙሪያ በተካሄደ ዳሰሳ ጥናት በፕሮጀክቱ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች እና የማህበራዊ ልማት ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ልማት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ታደሰ DRDIP በክልሉ በ5 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደሮች 45 ቀበሌዎች ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ ለማህበራዊ ተቋማት ግንባታና ተያያጅ የማህበረሰብ ልማት ስራዎች በዓመት እስከ 1 ቢሊየን ብር በጀት መድቦ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።
በዚህም ላይ ተጠቃሚ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በተዘረጉ የአሰራር ስርዓቶች መሰረት ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር በመናበብ በፕሮጀክቶቹ በአግባቡ እንዲጠቀሙም ጠቁመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር የልማት ፕሮጀክቶች ሲመጡ የመንግስትን የልማት ክፍተቶች ለመሙላትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሻሻል መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶቹን በአግባቡ በማስተባበርና በመጠቀም የአካባቢያቸውን ልማት ያሻሻሉ ወረዳዎች እንዳሉ ሁሉ የፕሮጀክቱን አላማ በአግባቡ ባለመረዳትና ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት የተመደበላቸውን በጀት የሚያባክኑ እንዳሉም ጠቁመዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የፕሮጀክት ተጠቃሚ ወረዳዎችና በተባባሪነት የሚፈጽሙ ተቋማት በተቀመጡ የአሰራር መመሪያዎች መሰረት ክትትል በማድረግ የሚገኘዉን እድል ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት እንዲያውሉ አሳስበዋል።
በመድረኩም የሙስና ጽንሰ ሀሳብ፤ በፕሮጀክቶች የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችና መፍትሄዎቻቸው በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ሰነዶቹ በኮሚሽኑ የፊት ለፊት የሥነ-ምግባር ሥልጠና ባለሙያዎች አቶ ገዛኸኝ የኔው እና አቶ አወቀ ገ/መስቀል እንደ ቅደም ተከተላቸው ቀርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *