በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግንባታ ሂደታቸው የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው፡- የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

ወቅታዊ መረጃ

 

(አሶሳ፣ ጥቅምት 20/2018 ዓ/ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሂደታቸው የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡

 

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሂደታቸው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ማስቀጠል ላይ ትኩረት ያደረገ የመስክ ምልከታ ኣሂደዋል።

 

በአሶሳ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ስር ከሚገኙት የመንገድ ኘሮጀክቶች መካከል የአሶሳ – ዳለቲ – ባሮዳ (ሎት አንድ ) እና የሆሞሻ – ህዳሴ የመንገድ ፕሮጀክቶች ይገኙባቸዋል፡፡

ግንባታው ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የአሶሳ – ዳለቲ ባሩዳ (ሎት አንድ) የግንባታው አፈጻጸሙ ሰባ በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውሷል፡፡

 

የመንገዱን ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የስራ ተቋራጭ ሰናን ኮንስራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር ሲሆን፣ የስራ ተቋራጩ አፈፃፀም ደካማ መሆን እና በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ሁኔታ ለፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ምክንያት መሆኑንም አስተዳድሩ ጠቅሷል፡፡

 

ይህን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር ችግሮችን ለመቅረፍና ፕሮጀክቶቹን ወደ ስራ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አንስቷል፡፡

 

በሥፍራው በመገኘት በተደረገው ውይይት በሥራ ተቋራጩ በኩል ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ የመንገድ ስራው ላይ የሚያስፈልጉ የኮንስትራክሽን ግብዓት እና የነዳጅ አቅርቦት በተገቢው ጊዜ ቀርቦ ወደ ስራ  እንዲገቡ፣ አስፋልት ለማንጠፍ የሚያስችሉ  የሰብቤዝ እና የቤዝኮርስ ጠጠሮችን አምርቶ ፕሮጀክቱን ለማፋጠን አስቻይ ሁኔታዎች ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ስምምነት ላይ መደረሱንም ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

በተመሳሳይ የሆሞሻ – ህዳሴ (ሎት አንድ) መንገድ ፕሮጀክት በሀገር – በቀሉ እንይ ኮንስትራክሽን ሲከናወን ቆይቶ ከጸጥታ እና ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ችግር ተቋርጦ መቆየቱን ጠቅሶ፣ አሁን ላይ በተደረጉ ጥረቶች ፕሮጀክቱ ወደ ግንባታ እየተመለሰ ሲሆን፤ በቅድመ-ዝግጅት ሂደት እንደሚገኝ ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው መስተጓጎል እንዳይገጥመው የጥገና ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ እና ሥራው እንዲቀጥል በቦታው ባደረጉት የመስክ ቅኝት ወቅት አቅጣጫ ሰጥተዋል።

 

ይህ ፕሮጀክት ወረዳዎችን ከቀበሌዎች በማስተሳሰር ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብር የሚያጠናክር ከመሆኑ በተጨማሪ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እንደ አማራጭ መንገድ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡

 

በክልሉ የሚገኙ ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶችንም በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።

 

 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *