የኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባራት

በሌሎች ህጐች ለኮሚሽኑ የተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው ኮሚሽኑ የሚከተሉትን ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡፡

  • ሙስና ያለውን ጎጅነት በተመለከተ የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና እንዲጎለብት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያስተምራል፣ ለህዝቡ በሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ መልካም ሥነ-ምግባር እንዲስፋፋ በማድረግ ህብረተሰቡ ከሙስና እና ከብልሹ አሠራር እንዲቆጠብ ይሠራል፡፡
  • ሥነ-ምግባርና ሙስናን በተመለከተ የአሠራር ጥናትና ምርመራ ማድረግና ተመሣሣይ የሆኑ ሥራዎችን ይደግፋል፣ የኮሚሽኑን ዓላማዎች ለማራመድ የሚያገለግሉ ትምህርት ሰጪ ህትመቶችን፣ ራፖርቶችንና የቴክኒክ ጥናቶችን በማሳተም ያሰራጫል፡፡
  • ለክልሉ ህብረተሰብ የሥነ-ምግባር ትምህርት ይሰጣል፣ የፀረ-ሙስና ጥምረት ያቋቁማል፣ እንዲቋቋሙ ያደርጋል፣ ያስተባብራል፣ የሙያ ድጋፍ ይሰጣል፡፡
  • ስትራቴጅካዊ በሆነ አኳኋን በቅንጅት የፀረ-ሙስና ትግሉን በማድረግና በመከላከል ላይ በየደረጃው ባሉ የክልሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የፀረ-ሙስና ጥምረትና ሌሎች አደረጃጀቶች እንዲቋቋሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣ ይደግፋል፣ ይከታተላል፣ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለጠቅላላ ጉባኤ ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካል ያቀርባል፡፡
  • በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ህዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ወይም ሊያጋልጡ የሚችሉ የሥራ ሁኔታዎች ላይ ጥናት ያካሄዳል፣ እንዲጠኑ ያደርጋል፣ የአሠራር ሥርዓት መሻሻሉን ይከታተላል፣ እንደ አስፈላጊነቱ እርምጃ እንዲወሰድ ወይም ወሣኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከታው አካል ያሳውቃል፣ ያሳስባል፣ በሌላ አካል ሲጠየቅ ምክርና ተመሣሣይ የሆነ ድጋፍ ያደርጋል፣
  •  በህጉ መሠረት ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ሃብታቸውንና የገንዘብ ጥቅማቸውን እንዲያስመዘግቡ በህግ ግዴታ ያለባቸው ባለሥልጣናት፣ የህዝብ ተመራጮች፣ ተሿሚዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች ወይም በህግ ኃላፊነት ያለባቸው በተመለከተ ሃብት፣ ገንዘብና ጥቅማ ጥቅማቸውን መዝግቦ ማስረጃ ይይዛል፣ ተመዝግቦ ማስረጃ እንዲያዝ ያደርጋል፣ ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል፣ ሠርትፊኬት ይሰጣል፣ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡
  • የፀረ-ሙስና ህጎች እና የሥነ-ምግባር ደንቦች መከበራቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፣ የፀረ-ሙስና ህጎችና የሥነ-ምግባር ደንቦች ከተጣሱ የሥነ-ምግባር እርምጃዎች እንዲወሰዱ ሌሎች የሥነ-ምግባር ማስፋፊያ አካላትን ያስተባብራል፣ ይደግፋል፣
  •  ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ለህዝባዊ ድርጅቶች የሚያገለግል የሥነ-ምግባር ደንብ እንዲዘጋጅ ያደርጋል፣ መዘጋጀቱን ያረጋግጣል፣ የሙያ ድጋፍ ይሰጣል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፣
  • የፀረ-ሙስና ትግል በማካሄድ እና በመከላከል ሂደት ውስጥ መልካም ውጤት ያስመዘገቡ ሰዎች፣ መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት የሚመዘኑበት እና የሚሸለሙበት ሥርዓት ይዘረጋል፣ ሲፀድቅ ሥራ ላይ ያውላል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፣
  • ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ከሌሎች የክልሉ እና የፌዴራል አካላት ጋር አስፈላጊ የሆነ ግንኙነት ትብብር ይፈጥራል፣ በክልሉና በሀገሪቱ ህግና ፖሊሲ መሠረት የተደረጉትን ስምምነቶች ያስፈፅማል፣
  • አስፈላጊ ከሆኑ አካላት ጋር በመተባበር የሥነ-ምግባር መከታተያና ማስፋፊያ አውታሮችን ያስተባብራል ለዚህ ዓላማ የሚያስፈልጉ የተለያዩ የፀረ-ሙስና አደረጃጀቶች እንዲቋቋሙ ያደርጋል፣
  • የሥነ-ምግባር መከታተያና ማስፋፊያ ክፍሎች አደረጃጀትና አሠራርን በተመለከተ መመሪያ ያወጣል፣ ይከታተላል፣
  • ሀብት ያፈራል፣ የተለያየ ውል ይፈፅማል፣ ይከሳል፣ ይከሰሳል፣
  • የኮሚሽኑን ዓላማዎች ከግቡ ለማድረስ የሚያረጋግጥበት የአሠራር ሥርዓት ይዘረጋል፣
  • የኮሚሽኑን ዓላማዎች ከግቡ ለማድረስ የሚረዱትን ሌሎች ሥራዎችን ይፈፅማል