እንደክልል የሚስተዋሉ የመንገድ ደሕንነት እና የትራፊክ ቁጥጥር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የጥናት ግኝት ለውይይት ቀረበ፡፡
በክልሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የጥናት ባለሙያዎች የተሰራ እንደክልል የሚስተዋሉ የመንገድ ደሕንነትና የትራፊክ ቁጥጥር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ጥናት ለውይይት ቀረበ፡፡
የጥናት ግኝቱን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ያቀረቡት አቶ ሰገድ ስዩም ፣ የጥናቱ ዋና ዓላማ በመንገድ ደሕንነት እና የትራፊክ ቁጥጥር የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በመፈተሸ የዕርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ለማመላከት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በጥናቱ ግኝት ለሙስናና ብልሹ አሰራሮች የተጋለጡ ተብለው ከተጠቀሱ 12 አሠራሮች መካከል፤ መንግስት ካወጣው ታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ያለታርጋ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች መኖራቸው፣ የተሸከርካሪዎች የቴክኒክ ምርመራ ወቅቱን ጠብቆ ያለማድረግ፣ የአሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርክር፣ ሕጋዊ መንጃ-ፈቃድ ሳይዙ ማሽከርከር እና የትራፊክ ፖሊሶች የተሰጣቸውን የሥራ ኃላፈነት በአግባቡ ያለመወጣት….የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በመድረኩ ተገኝተው ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት የሙስና መከላከል ዳ/ ዳይሬክተር አቶ ጊሳ ዚፉ፣ ኮሚሽኑ ከተሰጡት ዋና ዋና ተልዕኮዎች መካከል አንዱ ለሙስናና ብልሹ አሰራሮች የተጋለጡ አሰራሮችን በጥናት ለይቶ የማስተካከያ እርምጃዎችን ማስወሰድ መሆኑን ጠቅሰው የቀረበው የጥናት ግኝት ውጤት በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በጥናቱ ግኝት ላይ ችግሩን ለመቅረፍ በመፍትሄ ሃሳብነት የቀረቡ አቅጣጫዎችን በግብዓትነት ወስደው በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

