(አሶሳ፣ ጥቅምት 14/ 2015 ዓ.ም) የክልል የፀረ-ሙስና ኮሚቴ ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ የክልሉ ፍትህ ቢሮ እና የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡ በፍትህ ቢሮ በኩል ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት አቶ ሰይድ ባብከር የኮሚቴው ሰብሳቢና የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ኮሚቴው ወደ ስራ መግባቱን ገልፀው፤ ከዚህ በፊት የፀረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግም የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙንና ስራ መጀመሩን አንስተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሙስናና ብልሹ አሰራር የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ልዩ ምርመራና ልዩ ዐቃቤ እንዲሁም ልዩ ችሎት ኮሚቴው የሚጠቀም መሆኑን እና ቀደም ሲል የተጀመሩ የሙስና ምርመራ ሂደቶች የሚያስቀጥሉና አዳዲስ የሙስና ጥቆማዎች በመቀበል ስራዎች እንደሚሰሩ በጋዜጣዊ መግለጫው ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡ 9080 ነፃ የሥልክ መስመር በመጠቀም የሙስና ጥቆማ በድምፅ ጥሪና በመልዕክት ማድረስ እንደሚችል የገለፁት አቶ ሰይድ ባብከር ጥቆማ ሰጭዎች ከብቀላ ነፃ የሆኑ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃዎችን እንዲያደርሱ አሳስበው፤ ለጠቆሚዎች ጥበቃና ከለላ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ ከሙሰኞች ጋር የሚያደርገው ትንቅንቅ ውጤታማ እንዲሆንም ማህበረሰቡ ለኮሚቴው መረጃ በመስጠት እና በልዩ ልዩ መንገድ እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል የፀረ-ሙስና ኮሚቴው አላማ ሙሰኞችን ተጠያቂ በማድረግና የተመዘበረ የመንግስት ሃብትና ንብረት በማስመለስ የተደራጀ ሌብነት (ሙስና) በክልሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበረዊ መስተግባር ላይ የሚያደርሰውን ችግር መግታት መሆኑን አቶ መንግስቱ ላሎ (የክልሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የኮሚቴው አባል) ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴዎች በሂደትም በዞንና በወረዳዎች መልካም ስነ-ምግባር ባላቸውን አካላት በየደረጃው ሊቋቋም እንደሚችል አንስተዋል፡፡
አክለውም ማህበረሰቡ የሚያማርርባቸው የተለያዩ ዘርፎች መለየታቸውን የገለፁት ኮሚሽነር መንግስቱ በተለይም ከማዕድን፣ ንግድ ዘርፍ፣ ከገጠር መሬት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ አፈፃፀሞች ፣ በቀበሌ ደረጃ የመታወቂያና የስራ አጥ ማስረጃ አሰጣጥ በልዩ ሆኔታ የሚታዩ መሆኑን እና ውጤታማ ስራ እንደሚሰራ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይህ ስራ ውጤታማ እንዲሆንም ማህበረሰቡ በእጅ መንሻ በመሄድ አገልግሎት ለማገኘት ከመሞከር እራሱን በማቀብ በሌብነት የተዘፈቁ አካላትን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቋሚዎች መረጃ ሲሰጡም በአዋጅ ቁጥር 103/2004 አንቀፅ 20 (4) መሰረት በእርግጥም ሙስና መፈፀሙ ከተረጋገጠ በሙስና ከተመዘበረው ሃብት 25 ከመቶ ለጠቋሚው የሚሰጥበት አሰራር ተፈፃሚ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡የክልሉ ማህበረሰብ ጥቆማ የሚሰጥባቸው ሌሎች የማህበራዊ የሚዲያ አማራጮች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ ለክልሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ፍትህ ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን በአካል በመቅረብ ጭምር መረጃና ማስረጃዎችን መስጠት እንደሚችሉ አሳስበዋል፡፡
