
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የስነ-ምግባር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት በሥነ-ምግባር የታነፁ፤ ሙስናን የሚፀየፉ ፓርቲውና መንግስት የሰጣቸውን ኃላፊነት እና ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ በሚሰራው ስራ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በሥነ-ምግባር የታነፀና ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚታገል ማህበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጥረትም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በትብብር እንደሚሰራ የፓርቲው የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ስንታየሁ አበበ በተለይም የሁለቱን ተቋማት ቀጣይ የስድስት ወር የጋራ እቅድ በኮሚሽኑ ጽ/ቤት ተገኝተው ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
እቅዱ በጋራ የሚያሰራና ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን የገለፁት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽር ከማል ሃሰን በበኩላቸው፤ እቅዱ የሚያሰራ መሆኑን ገልፀው፣ በፓርቲው ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከለካል የተሰጠው ትኩረት የፀረ-ሙስና ትግሉ እየተሻሻለና እየተጠናከረ መምጣቱን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡
መንግስትና ፓርቲው በተለይም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል አሰራሮችን እያሻሻለና እያዘመነ መምጣቱ ለዚህ አንዱና ሌላው ማሳያ እንደሆነም ኮሚሽር ከማል ሃሰን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መድረክ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከልና ተያያዥ በሆኑ የፀረ-ሙስና የትግል አቅጣጫዎች ላይ ከሁለቱ ተቋማት የተወጣጡ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ሰፊ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና የክልል ብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
