በማዕድኑ ዘርፍ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች (ጉዳይ ማጎታተት፣ የፍቃድ አሰጣጥ፣ ከህገ ወጥ ደላሎች ጋር የጥቅም ትስስር መፍጠር ) እና የመሳሰሉት መንግስት በዘርፉ የሚያገኘውን ጥቅም የሚያሳጣ፣ ለሃገርና ለማህበረስብ ዕድገት እንቅፋት የሚፈጥር፣ ለሰላም መድፍረስ በር የሚከፍት መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ ገልፀዋል፡፡
ዘርፉ ብዙ ፍላጎቶች የሚስተዋሉበት በመሆኑም በጠንካራ የሥራ ስነ-ምግባር መመራት ክፍተቶችንም መሙላት እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አክለው ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ በበኩላቸው ተቋሙ በፊት በኤጀንሲ ደረጃ ከነበረበት ሁኔታ በርካታ መሻሻሎች መኖራቸውን ገልፀው፤ አሁንም በአሰራር ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን ቢሮው እንደሚፈትሽና የማስተካከያ ስራዎችንም እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ትልልቅ ማማለያ ገንዘቦችን እምቢ የሚል ስብዕና ከእመነታችንና ከተሰጠን አደራ ጋር አያይዘን መገንባት እስከምንችል እራሳችንን መፈተሸና መገምገም፤ እኔ ማን ነኝ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፤ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኃላፊው መሰል ክፍተቶችንም ለመሙላት ቢሮው ከክልሉ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በቅርበት በመስራት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ቢሮው እንደ ሃገር ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአለም የፀረ-ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ – ሙስና ትግል፤ የነገን ስብዕና ይገነባል!” በሚል መሪ ቃል ያከበረ ሲሆን በዚህ መድረክ ለውይይት መነሻ እንዲሆን በኮሚሽኑ ከዘህ በፊት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በቢሮው የተጠና የጥናት ሰነድ ከፀረ-ሙስና ቀን መሪ ቃል ጋር ተዋዶ፤ ከቢሮው ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሂዶበታል ፡፡
ሰነዱን የኮሚሽኑ የፊት ለፊት የሥነ – ምግባር ሥልጠና ባለሙያ አቶ አወቀ ገ/መስቀል አቅርበውታል፡፡
