በክልሉ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

ወቅታዊ መረጃ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክልሉ ተወካዮች ገለጹ።

 

የሕዝብ ተወካዮቹ ከሕዝቡ በተነሱ የሠላም፣ የመሠረተ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ዙሪያ ላይ ያተኮረ የማጠቃለያ ውይይት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በተገኙበት አካሂደዋል፡፡

 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የክልሉ ተወካይ አቶ ሙባረክ ኤልያስ የመስክ ምልከታ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ክልሉ የነበሩ ውስብስብ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆኑ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።

 

በክልሉ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የተጀመሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በፌዴራል መንገዶች አስተዳድር በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እንዲሁም የሕዝብ ጥያቄዎች የሆኑት የትምህርት፣ የውሃ፣ የጤና ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ መንግስት ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን በተሰራው እልህ አስጨራሽ ስራ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

ሠላሙን ተከትሎ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በርካታ ርቀቶችን መሄድ መቻሉን አመላክተዋል።

 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሉ ተንቀሳቅሰው ከመረጣቸው ህዝብ ጋር  ውይይት በማድረግ ከህዝቡ የተነሱትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መንግስት በዕቅድ በመያዝ ደረጃ በደረጃ ይፈታልም ብለዋል።

 

የክልሉ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎች በርካታ እምርታዎች መመዝገቡን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተጀመሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲጠናቀቁ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

 

የህዝቡን አብሮነትና አንድነት ለማጎልበትም የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚሰሩ መናገራቸውን  የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ዘገባ ያመላክታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *