ባለፉት አምስት አመታት ከ 93 ሚሊዬን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡ኮሚሽኑ የአምስት ዓመት (2013-2017 ዓ.ም) እቅድ አፈጻፀሙን ዛሬ በኮሚሽኑ ጽ/ቤት በገመገመበት ወቅት እንዳስታወቀው ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ስልታዊ እቅድ ነድፎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ተወስቷል፡፡
በዚህም መሰረት በሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል በተሰራ ስራ 93, 583, 300 ብር ከምዝበራ በማዳን ለህዝብና ለመንግስት የልማት ስራዎች እንዲውል መደረጉን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይም በትምርትና ስልጠና፣ በሐብት ማስመዝገብና ማሳወቅ፣ በአሰራር ጥናት፣ በአውታሮች አደረጃጀት እና ተያያዥ የሙስና መከላከል ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
የተገኘው ውጤት አበረታች ነው ያሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ከማል ሀሰን በቀጣይ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ስልታዊ ግቦች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ገልፀው፤ ለውጤታማነቱም የጋራ እርብርብና ጥረት እንደሚጠይቅ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኮሚሽኑን የአምስት አመት እቅድ አፈጻፀም ያቀረቡት የኮሚሽኑ የዕቅድ፣ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ቶሎሳ ጅግልዱ ናቸው፡፡


