
**************
(አሶሳ፣ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም) የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመርቀን በአብሮነት በደመቅንበት ማግሥት የሚከበር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ አስታወቁ።
አክለውም የላብ፣ የውሃና የደም ጠብታ ውጤት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ የአባቶቻችንን ታሪክ አድምቀን የጻፍንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የሃገራችን የሉዓላዊነት እና የነጻነት ምልክታችን ነው ያሉት ወ/ሮ አስካለች፣ ብሔራዊ አርማ ለሆነው ሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር መስጠት ተገቢም አስፈላጊም መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 18ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጲያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ ቃል በክልሉ መስተዳድር ግቢ ተከብሯል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እና የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ እለቱን ምክንያት በማድረግ ሰንደቅ ዓላማ የማውጣት ሥነ-ሥርዓት ፈፅመዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎችና የፀጥታ አካላት የተገኙ ሲሆን፤ ለሁነቱ የክልሉ የፖሊስ ማርች ባንድ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥተውታል፡፡
