ተቋማት የአሰራር ግልፀኝነት በመፍጠር በተገልጋዮች ላይ ሚደርሰውን መጉላላት ሊቀንሱ ይገባል –  ኮሚሽነር ከማል ሃሰን

ወቅታዊ መረጃ

 

 

ተቋማት የአሰራር ግልፀኝነት በመፍጠር፤ በተገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን እንግልትና የጊዜ ብክነት በመቀነስ የተሻለ አገልግሎት ለዜጎች ማቅረብ እንደሚገባቸው  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ከማል ሃሰን አስታወቁ፡፡

 

በአንዳንድ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተገልጋዮች  አገልግሎትን ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች በግልፅ እንደማይነገሯቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ይህም ተገልጋዮችን  ለእንግልት በመዳረግ የእጅ መንሻ እንዲሰጡ እያስገደዳቸው መሆኑን  ተናግረዋል፡፡    አያይዘውም   ተቋማት እራሳቸውን በመፈተሸ  የአሰራር ግልፀኝነት  መፍጠርና   የተሻላ አገልግሎትን ለዜጎች ማድረስ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

 

ኮሚሽነር ከማል ሃሰን ይህን ያሉት በኮሚሽኑ የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና መድረክ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ መድረክ  በወረዳዎችና በተቋማት የተመደቡ የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎች አሰራሮች  አዋጅ፣  ደንብና መመሪያ ጥሰዋል ብለው ሲያምኑ መረጃዎችን በማደራጀት  ለኮሚሽኑ  የማሳወቅ  ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው ተወስቷል፡፡

 

በተያያዘ ዜና ሙስና ከኑሮ ውድነት ጋር ማያያዝ የተሳሳተና መገራት ያለበት አመላከከት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሙሰኝነት፤ ሕሊና ቢስነት ሲያልፍም ከሃይማኖት አስተምሮና ቀኖናና መውጣት መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡  ሙስናና ብልሹ አሰራርን መፀየፍ ለህሊናና ለሐይማኖታዊ ትዕዛዞች መገዛት፣ የዜግነት ግዴታን መወጣት መሆኑንን ልብ ማለት እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል፡፡

 

 

ሙስናና ብልሹ አሰራርን በዘላቂነት ለመከላከልም መንግስት አሰራሮችን እያዘመነ መሆኑ የተነሳ ሲሆን ሞሰብ የአንድ አገልግሎት ማዕከል በማሳያነት ተገልጧል፡፡ መሰል አሰራሮችን ማስፋትና አሰራሮች ዲጅታላይዝ ማድረግም ከተቋማት እንደሚጠበቅ በውይይት ዳብሯል፡፡

 

ስልጠናውን አቶ ጥላሁን በሲዞ (የኮሚሽኑ የአሰራር ጥናት ባለሙያ)፣ አቶ  አወቀ ገ/መስቀል እና አቶ ንጋቱ ጌታሁን (የኮሚሽኑ የትምህርትና ስልጠና  ባለሙያዎች)፤  በገቢዎች አስተዳዳር የአገልግሎት ለህቀት፣ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎች፤ የሙስና መከላለያ ስልቶች እና የሙስና ፅንሰ ሃሳብ በሚሉ ይዘቶች እንደየቅደም ተከተላቸው ሰጥተዋል፡፡

 

 

ኮሚሽኑ ለኢኮኖሚ ዘርፍ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎች እና ለክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን የኮምዩኒኬሽን እና የስልጠና ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማሻሻል ያለመ  ስልጠና ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *