
መንግሥት በ2018 ዓ.ም ለሕዝብ የቀረበና ለሕግ የታመነ ሕዝባዊ አስተዳደርና አገልግሎት ለመገንባት፤ ከዘጠኝ በመቶ በላይ ዕድገት ለማስመዝገብ እና 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና በሕዝቡ ተዓማኒነትን እንዲያተርፍ ትኩረት ሰጥቶ አንደሚሰራ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳነት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
ፕረዚዳንት ታዬ 6ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ መንግሥት ለኅብረተሰቡ የቀረበ እና እንግልት የሚቀንስ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት አሠራርን ለማሳደግ አበክሮ ይሰራል፡፡ ወደ በለፀገች ሀገር ለመሸጋገር ለሕዝብ የቀረበና ለሕግ የታመነ አስተዳደር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥታዊ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ በቅልጥፍና የታጀበ መሆን እንዳለበትም አመልክተው፤ የመንግሥት አስተዳደርና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የብዝኃነት ማዕከል እንዲሆኑ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
ለሕብረተሰቡ የቀረበ እና እንግልትን የሚቀንስ ሁሉን አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ዲጂታል በሆነ መልኩ ለመስጠት የተጀመረው ‘‘የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት’’ ተጠናክሮ እና ተስፋፍቶ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት፡፡
መልካም አስተዳደር የመልካም ፖለቲካ ማዕዘን ድንጋይ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ ፤ የሕዝብ አገልግሎት ለማዘመን በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በመመራት አመርቂ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በ2030 ዲጂታል ስትራቴጂ ደግሞ ይህንን ውጤት ወደ ልኅቀት በመለወጥ ሽግግር ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ – ቁጥር 027፣ ከመስከረም 27 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ዕትም ገፅ 1 ላይ የተወሰደ፤
