እንደ ሀገር የተጀመረው ወጥ የሆነ የዕቅድ እና ሪፖርት ሥርዓት የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
በፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የተመራ የሚኒስቴሩ ልዑክ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በተገኙበት ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በኢትዮጵያ ስታስቲክስ ልማት ፕሮግራም፣ በክልሎች የኢኮኖሚ አካውንት፣ ዕቅድ እና ሪፖርት ማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሀብቶች መገኛ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሀብቶች ለማልማት በተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በግብርናው ዘርፍ ብቻ 990 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፀው፤ ክልሉ በተለይ በማዕድን ሃብት ያለው አቅም ለሃገር ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
እንደሀገር እየተሠራ ያለው የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት ትግበራ፣ እየተመዘገበ ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂነት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት በአግባቡ ገምግሞ ወደ ሥራ መግባት እና ፕሮጀክቶችን ጨርሶ መጀመር ውስን ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሃገር ልማትና እድገት የራሱን ሚና የሚጫወት ክልል መሆኑን የገለፁት የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሀገር በሁሉም ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ልማት ከክልሎች ጋር አቀናጅቶ ለመምራት፤ የዘመነና ወጥ የሆነ የዕቅድ እና ሪፖርት ስርዓት ተዘርግቶ በፌዴራል ደረጃ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ገፅ ለገጻችን እንዲያመች ተደርጎ የተወሰደ ፤
