በክልሉ አዲሱ የመንግስት ሠራተኞች የመስከረም እና የጥቅምት ወራት የደመወዝ ጭማሪ ልዩነት ውዝፍ ክፍያ ከዛሬ ጀምሮ ለተቋማት እንደሚተላለፍ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ  

ወቅታዊ መረጃ

 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመንግስት ሠራተኞች የተፈቀደው የመስከረም እና የጥቅምት ወራት የደመወዝ ልዩነት ውዝፍ ክፍያ ከዛሬ ጀምሮ ለተቋማት እንደሚተላለፍ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ፡፡

 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ጉዳዩን አስመልክተው ለሚዲያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ መንግስት ከመስከረም 01/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉንም የመንግስት ሠራተኞች ያካተተ የደመወዝ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

 

በክልሉ የደመወዝ ክፍያውን ለመተግበር የሚያስችል ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመው፣ ለሠራተኞች በወቅቱ ደብዳቤ ማድረስ ማቻሉን አንስተዋል፡፡

 

በዚህ ሂደትም በክልሉ ያለው የመንግስት ሠራተኞች ቁጥር እና የፌዴራል መንግስት የፈቀደው በጀት አለመጣጣሙን ተከትሎ የደመወዝ ጭማሪ ልዩነቱን በወቅቱ መክፈል አለመቻሉን ያነሱት አቶ ጌታሁን፣ ይህ የሆነውም የመረጃ ማጥራት ሥራዎችን ማከናወን በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡

 

መሠል ችግሮች በተለያዩ ክልሎች መፈጠራቸውን ጠቁመው፣ በክልሉ ጉዳዩን ሌላ መልክ በማስያዝ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲናፈሱ የነበሩ አፍራሽ መልእክቶች እና አሉባልታዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ለመንግስት ሠራተኞች ተፈቅዶ በመረጃ ማጥራት ምክንያት ያልተከፈለውን የመስከረም እና የጥቅምት ወራት የደመወዝ ልዩነት ለመክፈል መወሰኑን ጠቁመው፣ ገንዘቡ ከዛሬ ጀምሮ ለተቋማት እንደሚተላለፍም ተናግረዋል፡፡

 

ከኅዳር ወር ጀምሮ ደግሞ በአዲሱ ደመወዝ ክፍያው እንደሚቀጥልም አቶ ጌታሁን ገልጸዋል፡፡

 

በክልሉ አሁንም የመንግስት ሠራተኞችን መረጃ የማጥራት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ ጌታሁን፣ በመረጃ ማጥራት ሂደት ለተፈጠረው መዘግየት በትዕግስት ለጠበቁት የመንግስት ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *