የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙሥና ኮሚሽን፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እና የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሀሰተኛ የት/ት ማስረጃ፣ የሙያ ፍቃድ፣ ንግድ ፍቃድና የመንጃ ፍቃድ በተመለከተ በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡
የክልሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ በፊርማው ሥነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት ሀሰተኛ ሰነዶችን የመለየት ሥራ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡
ይህም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚታየው የሕዝብ ዕሮሮ ምክንያት አገልግሎት እንዲሰጡ የተመደቡ አመራሮችና ባለሙያዎች በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተመደቡ በመሆናቸው የሚፈለገውን አገልግሎት የመስጠት የዕውቀትና የክህሎት ክፍተት ስላለባቸው መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር መንግስቱ ይህንን አጣርቶ እርምጃ መውሰድ የሚስተዋለውን የብልሹ አሰራር ሂደት ይቀርፈዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አየሁ እንዳሉት ሐሰተኛ የት/ት ማስረጃዎች በስፋት እየተሰራጨ መሆናቸውን እና በመንግስት ተቋማት በብዛት ሊገኙ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም የሰራተኞች የቅጥርና የምደባ ስርአቱ በሙስና እየተዘፈቀ የሚገኝ በመሆኑ በጋራ መስራታችን ይህንን ታግሎ በማሸነፍ ለማስቀረት ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱን መፈራረም ያስፈለገበት ምክንያት በሀሰተኛ የት/ት ማስረጃዎች ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ጉድለት በማስቀረት በየጊዜው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲቻል እና በጠንካራ ባለሙያዎች ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እንዲቻል መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ አብዱላዚዝ ተናግረዋል ፡፡

