ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
መታወቂያዎቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ማህተሞችና ወረቀቶችም በብርበራ ተይዘዋል፡፡
እንደ ፖሊስ መረጃ ፤ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ አካባቢ ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ለዚሁ ህገወጥ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚውሉ በአዲስ አበባ አስተዳደር ” የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር ጽ/ቤት ” እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎንደር ዞን ” ደባርቅ ከተማ የቀበሌ 01 አስተዳደር ጽ/ቤት ” የሚሉ ሃሰተኛ ክብ ማህተሞችን እንዲሁም የግለሰብ የስም ቲተር በማስቀርፅ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርማ ያረፈበትን የመታወቂያ ወረቀት አመሳስለው በማሳተም ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር ተገልጿል።
ማህተሞቹንና ወረቀቶቹን በአንድ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ደብቀው በማስቀመጥ የነዋሪነት መታወቂያ ለሚፈልጉ ሰዎች ሃሰተኛ መታወቂያዎችን እያዘጋጁ እንደሚሸጡ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል 3 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ነው።
ግለሰቦቹ ፤ ሃሰተኛ መታወቂያውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ማህተሞች ከተደበቁበት በብርበራ እንደተገኙም ፖሊስ አስታውቋል።
(አዲስ አበባ ፖሊስ)


Like
Comment
Share

