ኮሚሽኑ በመተከል ዞን በሚገኙ ተቋማት ለሚሰሩ ለአመራሮችና ባለሙያዎች አገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት የግንዘቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ኮሚሽኑ ባዘጋጀው በዚህ የስልጠና መድረክላይ መልዕክት ያስተላለፉት የመተከል ዞን ም/ አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ደበሎ አመራሮች ስልጠናውን እንደ ዞን ለውጥ ለማምጣትና የተሻለ አገልግሎት ለማድረስ እንደ ግብዓት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አመራችና ባለሙያዎችም ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ በማገልገል የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አቶ ፍቃዱ አስገንዝበዋል፡፡
በኮሚሽኑ የሐብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ወዲሻ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ሙስና በሀገርና በህዝብ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመቀነስና በዘላቂነት ለመከላከል በትውልድ ቀረፃና ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
የስልጠናው ዓላማም በዞኑ መምሪያ፣ በስራ ሂደትና በቡድን መሪዎች ደረጃ ያሉ የስራ ሃላፊዎች የመንግስት መመሪያና ደንብን ተከትለው ስራቸውን በስነ ምግባር እንዲፈፅሙ የሚያግዝ ነው ብለዋል አቶ ኤሊያስ፡፡ይህም የሙስና ወንጀሎችን ቀድሞ በአሰራር ሂደት ለመከላከል ያስችላል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤
በቀረበው ሰነድም አመራርና ባለሙያዎች በያዙት የስራ ኃላፊነት እውቀትና ክሎታቸውን በማቀናጀት ስነ ምግባር ተላብሰው ስራን መስራት ሲችሉ ከሙስና የፀዳ ውጤት ማስመዘገብ እንደሚቻል ተብራርቷል፡፡ ይህም የራስን ህይወት ከመቀየር ባለፈ የሀገር እድገትን እንደሚያፋጥን ተገልጿል፡፡
በመድረኩም የዞን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የስራ ሂደቶችና ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡


