ሕብረተሰቡ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ፍትህ ማግኘት እንደሚችል ማሳየት ይገባናል – የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ መሀመድ መሀሙድ

ወቅታዊ መረጃ

ኮሚሽኑ ከአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር  በፍርድ ቤቶች ስለሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሰራር ድርጊቶች፣  በር ስለሚከፍቱ የአሰራር ሂደቶችና መፍትሔዎቻቸውን በሚመለከት ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ  ዳኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

 

ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ   አገልግሎትን በማድረስ  ሕብረተሰቡ  ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ፍትህ ማግኘት እንደሚችል ማሳየት እንደሚገባ የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ መሀመድ መሀሙድ በዚህ ወቅት ገልፀዋል፡፡

 

በስልጠናው የተነሱ ጉዳዮችን ወደ እራስ በመውሰድም እራስን መፈተሽና ማስተካከል እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡

 

ሥነ-ምግባር የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት አቶ መሀመድ መሀሙድ የተትረፈረፈ እውቀትና አቅም በሥነ-ምግባር ካልተመራ ትርጉም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የስነ-ምግባር ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤቶች ሲመጣም ድርብ ኃላፊነት እንደሚሆንና የፍትህ ዘርፉ በጥብቅ ሥነ-ምግባር መመራት እንዳለበተ አሳስበዋል፡፡ ለተግባራዊነቱም አበክሮ መስራት እንደሚገባ ነው፤  አፅንኦት የሰጡት፡፡

 

ሥልጠናውን የሰጡት በኮሚሽኑ የፊት ለፊት የሥነ-ምግባር ትምህርትና ሥልጠና ኬዝ ቲም  አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ የኔው ሥነ-ምግባር በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ የትክክለኝነትና የስህተት መለኪያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ በሚመለከት ተገልጋዮችን በማነጋገር የተሰራ አጭር ዳሰሳ ዋቢ በማድረግ ተገልጋዮች ባቀረቧቸው ክፍተቶች ላይ መሰድ ስለሚገባቸው መፍትሄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

ስልጠናው ከስራቸው ጋር የሚሄድ፣ የሚያነቃቸውና የሚያጠናክራቸው መሆኑን የገለፁት ተሳታፊዎች  መሰል ሥልጠናዎች ተከታታይነት እንዲኖራቸው   ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *