የፕሮጀክቶችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል – ም/ኮሚሽነር ነጅመዲን አልመሐዲ
በክልሉ የመንገድ ተደራሽነትን በማስፋፋት የማህበረሰብን ኑሮ ማሻሻልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ታልመው በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚጠገኑ/የሚሰሩ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ም/ኮሚሽነር ነጅመዲን አልመሐዲ ገለፁ፡፡
ም/ኮሚሽነሩ አክለውም በቅንጅት መስራት፣ አደረጃጀትን ማጠናከርና ቀጣይነት ያለው የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ነው፤ አጽንኦት የሰጡት፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተተገበረ ባለው የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ከአቡርሐሞ፣ አበንዴ፣ ሸርቆሌ አወፈንዱ እና ከሸደርያ፣ ቡልድግሉ፣ አቡርሐሞ እየተጠገኑ ያሉ መንገዶችን በሚመለከት ኮሚሽኑ ከክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ለውይይቱ መነሻ ማህበረሰብን በማወያየት በጥንካሬና በድክመት የተለዩ ግኝቶችንና የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦችን በሚመለከት በኮሚሽኑ የስልጠና ባለሙያ አቶ አወቀ ገ/መስቀል አጭር የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡
በዚህ መድረክ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሙኒየም አደም በዳሰሳ ጥናቱ የተለዩ ክፍተቶችን ለማረም የተግባር እርምጃዎች እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ጥራት በሚመለከት ኮሚሽኑ ከክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በቅርበት መስራቱ መጠናከር እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው


