ኮሚሽኑ ከፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የአቻ ለአቻ ድጋፋዊ ግምገማ ለማድረግ ከመጣው ቡድን ጋር የመጠቃለያ ውይይት አድርጓል፡፡
ተቋሙ በክልሉ በሚገኙ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ሙስናና ብልሹ አሰራርን ቀድሞ ለመከላከል የአስራር ጥናትን እንደ አንድ ቁልፍ መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑን ኮሚሽነር ከማል ሃሰን በውይይቱ አውስተዋል፡፡
በዚህ ስራም ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ የሆኑ የመንግስት ተቋማት ካላቸው የስራ ባህሪና ከተገልጋዮች በሚደርስ ጥቆማ እንደሚለዩ እና ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ የአሰራር ሂደቶች እንዲዘጉ የማጥናት፣ የማማከር፣ የድጋፍና የክትትል ስራዎችን እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
በዚህም ለሙስናና ብልሹ አሰራር ተጋላጭ በሆኑ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች የህዝብና የመንግስት ሃብትና ንብረትን ከምዝበራ በማዳን ለታለመለት አላማ እንዲውል በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም የተቋሙን የአሰራር ጥናት ባለሙያዎች ቁጥር ማሳደግና ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅደም ተከተል መፍታት አንደኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የምልከታ ቡድኑ በበኩሉ በኮሚሽኑ በርካታ ጠንካራ ጎኖችን ማስተዋሉን ገልፆ መስተካከል በሚገባቸው ውስንነቶች ላይ አስተያዬት ሰጥቷል፡፡
2ኛው አገር ዓቀፍ የኮሚሽኖች የአቻ ለአቻ ድጋፋዊ ምልከታ (ሱፐርቪዥን) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግባና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ከፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመጣ ቡድን እየተካሄደ መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
