ወቅታዊ መረጃ

ለራሳችሁ የምትመኙትን ለሌሎችም እንዲሆን እስካልተመኛችሁ ድረስ በትክክል አላመናችሁም (የነብዩ መሐመድ ተግባራትና ንግግሮች )

እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው ህግም ነቢያትም ይህ ነዉና (ክርስትና / ማቴ 7፣12)

ሥለዚህ ወጣቶች እለት በእለት በሚያደርጉት ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ወርቃማ ግብረገባዊ ህጎች (Golden rules of morality) መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን በወጣቶች ለሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ግድፈቶች የቴክኖሎጂና ማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖ፤ የሀይማኖትና የባህል ተጽዕኖ መቀነስ – የሞራል መመሪያ መሠረቶች መዳከም፤ ፈጣን ለውጥና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ – ባህላዊ እሴቶች ከዘመናዊ እሴቶች ጋር መጋጨት ከብዙ በጥቂቱ ገፊ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ከላይ ለወጣቱ የሥነ-ምግባር መጓደል ምክንያት ከሆኑ ተፅእኖዎች ወጣቱ እራሱን ለመጠበቅም፤ ራስን መቆጣጠር ፣ በታማኝነትና ፍትሃዊነት ህይወትን መምራት ፣ ትምህርትና እውቀትን መሻት ፣ ሕግን ማክብር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህ ሳይሆን ቢቀር ማለትም ወጣቶች እራሳቸውን በመልካም ሥነ-ምገባር ካላረቁ /የመልካም ሥነ-ምገባር ባለቤት ካልሆኑ የትምህርት ውጤት ዝቅተኛ መሆን፣ ትኩረትን የማጣት እና የአደንዛዥ እፅ ሱስ ውስጥ መግባት ከዚሁ ጋር የተያዙ የጤና ችግሮች ሰለባ የመሆን የግል ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡

በማህበራዊ መስተጋብራቸውም ከማህበረሰብና ቤተሰብ የመነጠል እና እምነትን የማይጣልባቸው እንዲሆኑ ያደርጋል፤ ይህም ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ችግር ይዳርጋቸዋል፡፡

ከዚህ አልፎ ወጣቶች በመልካም ሥነ-ምገባር የታነፁ ካልሆኑ የህግ ተጠያቂነትና የዲስፒሊን ቅጣቶች ሊያጋጥሞቸው ይችላሉ፡፡

የሥራ እድል ማጣት – የስም መጉደፍ ፣ የሀላፊነትና የመሪነት እድል ማጣትም በወጣቶች ቀጣይ ህይወት የሚያጋጥም ሌላው የመልካም ሥነ-ምግባር ባለቤት ያለመሆን ዳፋ ይሆናል፡፡

ወጣቶች በሥነ-ምገባር ካልታነፁም ዳፋው ከራሳቸው አልፎ የማህበረሰቡ የደህንነትና የሠላም ስጋት የመሆን አዝማሚያ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ሀገራት አንድ ትውልድ ትውልዳዊ ፍሰቱን ጠብቆ ዘመናትን በስኬት መጓዝ ይችል ዘንድ ከቁሳዊ ሥልጣኔ ባሻገር በመንፈስ የሰለጠነ፤ በሥነ ምግባር የታነፀና ባለራዕይ ትውልድ ያስፈልጋቸዋል የሚባለውም ሥነ-ምግባር ለሃገርና ለማህበረሰብ ያለውን የገዘፈ ጥቅም በማስተዋል ነው፡፡

ይህም መልካም ሥነ-ምግባርን መገንባት ፤ ማህበራዊ ሰላምንና እድገትን ለማጠናከር ፣ መተባበርን ያጎለብታል፤ ሙስናና ወንጀልን ለመከላከል እና ኃላፊነት ያለው ዜጋ ለመፍጠርም የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

በእነዚህና በሌሎች በርካታ አመክንዬዎች ወጣቶች ታማኝ፣ ትዕግሥኛ ፣ ታታሪ ፣ ሩህሩህ ፣ ፍትሃዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ያላቸው እንዲሆኑ መስራት ወጣቶችን ጨምሮ የዜጎች ሁሉ ድርሻ/የተቋማት ሁሉ ኃላፊነት መሆኑን የበርካታ ሃገሮች የመውደቅ መነሳት ልምዶች ይመሰክራሉ፡፡

በአላማችን በተለያዩ ጊዜያት ያለፉ ፈላስፎችና ሙህራንም ይህንኑ የወጣቶች መልካም ሥነ-ምግባር ባለቤት መሆን ያለውን በጎ ተፅእኖ በአባባሎቻቸውና በንግግሮቻቸው አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም
“የሰው ግብ መልካም መሆን ነው፤ መልካም መሆንም በሥነ-ምግባር ይጀምራል።”/አርስቶትል/
ሥነ-ምግባር የሕይወት ዓላማ መሠረት መሆኑን ይጠቁማል።

“ልጆችን ማስተማር ማህበረሰብን ማዳን ነው።”/ፕላቶ/
ወጣቶችን በሥነ-ምግባር ማስተማር የማህበረሰብ ደህንነት ነው።

ወጣቶችም ይህንን ተገንዘበው በዚህ መተየብ መነሻ በተገለፀው የሁለቱ እምነቶች ወርቃማ ህጎች እራሳቸውን መግራትና መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አቶ አወቀ ገ/መስቀል – የኮሚሽኑ የፊት ለፊት የሥነ-ምግባር ትምህርትና ሥልጠና ባለሙያ

በአሶሳ ግብርና ኮሌጅ ተገኝተው ከ700 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በትውልድ የስብዕና ግንባታ የሞራል እሴት አስፈላጊነት በሚል ርዕስ ከሰጡት ሥልጠና ለገጻችን እንዲያመች ተድርጎ የተወሰደ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *