በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋለው ብልሹ አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ምሬት እያመጣ በመሆኑ አስቸኳይ እና ወቅታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ….፡፡

-
የቤኒሻንጉል /ጉ/ክ/ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአሶሳ ከተማ ከሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አካሄደ፡፡
የውይይቱ መነሻ ሀሳብ የነበረው ‹‹ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራር ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው›› የተመለከተ በስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተሰራው የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡
የመድረኩ አላማ በንግድ ዘርፍ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር እና እያስከተለ ያለውን ችግር ነቅሶ ለማውጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየቱ የተሻለ እና የተረጋጋ የገበያ ስርአትን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ ከሚገባው በላይ ማትረፍ የስነ-ምግባር ጉድለት መሆኑ በውይይቱ ወቅት በዋናነት የተነሳ ሀሳብ ሲሆን በተለይ ሃገራዊ የጸጥታ ችግሮችን ተከትሎ የተፈጠሩ የመንገድ መዘጋቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ለወገን አለማሰብ እና ህሊና -ቢስነት መሆኑ ተሳታፊዎች የተስማሙበት ጉዳይ ነበር፡፡
ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት ከስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ፤ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ሐይማኖት ዲሳሳ እና ከክልሉ ንግድ ቢሮ አቶ ከማል መሀመድአሊ ኢብራሂም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በስነ-ምግባር ዙሪያ ቀጣይነት ያለው መድረክ በሦስቱ ተቋማት ቅንጅት ወደፊት እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *