ሌብነት አታካች ከመሆኑም በዘለለ በከፍተኛ ሁኔታ ለመንግሥት ፈተና እየሆነ መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
መንግሥት ‘ቀይ መስመር’ ብሎ ያሰመረውን ሌብነት፣ ሌቦች ‘ቀይ ምንጣፍ’ እያደረጉት ነው ብለዋል።
ሌብነት የኢኮኖሚ ነቀዝ እና የዕድገት ነቀርሳ ቢሆንም፣ አንዳንድ አካላት ግን ድርጊቱን እንደመብት እየወሰዱት በመሆኑ አደገኛ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በሌብነት ላይ ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረ ያለው ሌብነት የሠሚሩትን ሁሉ እየበላ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትርሩ፣ በማያዳግም ሁኔታ ችግሩን ለመፍታት ጥናቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱም ለእርምጃው አጋዥ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
እያንዳንዱ ዜጋም ሌብነትን በመዋጋት ሂደት በመጠቆሚያ አድራሻ ተገቢ ማስረጃ በማቅረብ የእርምት እርምጃው አካል ሊሆን እንደሚገበ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት መደረጉን እና ውሳኔው በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
(EBC)
