የሕክምና ባለሙያዎች በመልካም ሥነ-ምግባር ማህበረሰብን እዲያገለግሉ ጥሪ ቀረበ፡፡
ም/ኮሚሽነር ኦሳማ ከሊፋ የህክምና ባለሙያዎች ለሙስናና ብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ ሂደቶችን በማረም በመልካም ሥነ-ምግባር ማህበረሰብን ማገልገል፤ እንደሚገባ ገለፁ፡፡
ከሰሞኑ ተቋሙ በተለያዩ የጤና ተቋማት ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት የአገልግሎት አሰጣጥና የአሰራር ክፍተቶች መኖራቸውን ለይቷል፡፡
ይህንንም መነሻ በማድረግ ለመንጌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ መንጌ ጤና ጣቢያና የአቡጀንዱ ጤና ጣቢያ የህክምና ባለሙዎች፣ አመራሮችና የአስተዳደር ሰራተኞች የግንዛቤ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የኮሚሽኑ የፊት ለፊት የሥልጠና ባለሙያ አቶ አወቀ ገ/መስቀል በህክምናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ግድፈቶች፣ መፍትሔ እና የሚኖረውን የህሊናና የህግ ተጠያቂነት አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ከዚህ በፊት ሰፊ የአሰራር ክፍተቶች ይስተወሉ እንደነበር የገለፁት የሥልጠናው ተሳታፊዎች፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኮሚሽኑ የመከታተያ ክፍል በማስመደቡ እና በሚያደርገው ክትትል በተለይ በመንጌ ሆስፒታል የአሰራር መሻሻሎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ መሰል የስልጠና ድጋፎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡


