አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለተገልጋዮች ከአድሎና ምልጃ የፀዳ፣ ተገቢና ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል፡፡ ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ

ወቅታዊ መረጃ

አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለተገልጋዮች ከአድሎና ምልጃ የፀዳ፣ ተገቢና ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል፡፡
ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ

(ባምባሲ ህዳር 5/2017 ዓ/ም፤ የቤጉክ የሥ/ፀረ – ሙስና ኮሚሽን) አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለተገልጋዮች ከአድሎና ምልጃ የፀዳ፣ ተገቢና ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ አሳሰቡ፡፡

ኮሚሽኑ ከባምባሲ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የሥራ ስነ-ምግባርና ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ረገድ የባለድርሻ አካላት ሚና በሚሉ ሁለት ሰነዶች በከተማ አስተዳደሩ ለሚሰሩ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ መንግስታዊ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ዜጎችን በፍትሐዊነት እና በቅንነት ሊያስተናግዱ እንደሚገባ ተናግረው፤ ነገር ግን አሁንም ዜጎች መሰረታዊ አገልግሎትን ለማግኘት ወደ ተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሲሄዱ ጉቦ ይጠየቃሉ፣ ጉዳያቸውም ያላግባብ እንዲዘገይ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም ችግሩ የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲዳከም እንደሚያደርግና በህግ ጥበቃ የተደረገላቸው ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ ድንጋጌዎች እንዲጣሱ በር የሚከፍት በመሆኑ ተቋማት አሰራራቸው ከሙስናና ብልሹ አሰራር የፀዳ ስለመሆኑ እንዲፈትሹ አስገንዝበዋል፡፡

የባምባሲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ፈይሴል አሊ በበኩላቸው በአቋራጭ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ አካላትን የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ደንብን፣ መመሪያንና ህግን መሰረት አድርጎ በመስራት ሊያስቆሟቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዚህ መድረክ ግልፅነት የሚሹ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የኮሚሽኑ የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል ዳይሬክተር የራሥወርቅ መሰረት ምልሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የውይይት መነሻ ሰነዶችን በማቅረብ ሰፊ ማብራሪያ ያቀረቡት የኮሚሽኑ የሥልጠና ባለሙያዎች አቶ ገዛኸኝ የኔው እና አቶ አወቀ ገ/መስቀል ናቸው፡፡

 

በመልካም ሥነ-ምግባር የተገነባ ማህበረሰብ፤

ለጥቆማ – www.bgrseacc.gov.et
ፌስ ቡክ – https://web.facebook.com/bgrseacc
ቴሌግራም – https://t.me/bgrseaccpr
ዩቲዩብ – https://www.youtube.com/channel/UCLXoTV-dWDw1z7yNAPnbYYQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *