(አሶሳ ህዳር 13/2017 ዓ.ም፤ የቤጉክ የሥ/ፀረ – ሙስና ኮሚሽን) ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተቋማት ተግባራዊ ምላሽ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ አስታወቁ፡፡
ኮሚሽኑ ለአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኞችና አስተዳደር ሰራተኞች የሥራ ስነ-ምግባርና ለሙስናና ብልሹ አሰራ ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን ከብልሹ አሰራር መከላከል በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች የግንዛቤ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በዚሁ መድረክ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶችን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ጥናቶች መጠናታቸውን እና ምክረ -ሃሳቦች መቅረባቸውን የገልፁት ኮሚሽነሩ፤ ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ከተቋማት ቁርጠኛና ተግባራዊ ምላሽ እንደሚጠበቅ አስገንዝዋል፡፡
የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ተመስጌን ኃይሉ በበኩላቸው ኮሌጁ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ የአሰራር ሂደቶችን ለማረም የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበው፤ ኮሌጁ ከሰው ሃይል ቅጥርና አመራር ጋር ተያይዞ ለረጅም ጊዜ ሲስተዋል ነበረውን ብልሹ አሰራር ማስተካከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን የሠጡት በኮሚሽኑ የፊት ለፊት የሥነ-ምግባር ትምህርትና ስልጠና ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ የኔው ሲሆኑ ስራዎችን በመልካም ስነ-ምግባር መስራት የተቋማትን ውጤታማነት እንደሚያሳድግ፤ የሥነ-ምግባር ክፍተቶችን ለመሙላትም ተከታታይ የህይወት ክህሎት ስልጠናዎች መሰልጠን እና መልካም ልምምዶችን ማጎልበት መሰረታዊ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህ የግንዛቤ ስልጠና መድረክ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡


