በጥገና ላይ የሚገኙ የገጠር መንገዶች በተያዘላቸው የጥራት ደረጃና ጊዜ እንዲጠናቀቁ የክትትልና የድጋፍ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡

ወቅታዊ መረጃ
በጥገና ላይ የሚገኙ የገጠር መንገዶች በተያዘላቸው የጥራት ደረጃና ጊዜ እንዲጠናቀቁ የክትትልና የድጋፍ ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡
አቡርሐሞ፣ ግንቦት 15 /2017 ዓ.ም (የቤ/ጉ/ክ/መ/ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን) በአለም ባንክ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የገጠር ትስስር እና ተደራሽነት ፕሮግራም (RCAP) ከአሶሳ (ኢንዚ ሸደርያ) – አቡርሐሞ እንዲሁም ከአበንዴ ቀበሌ (አቡርሐሞ) – ሸርቆሌ – አፎንዴ የመንገድ ጥገና እየተካሄደ ነው፡፡
ከአሶሳ (ኢንዚ ሸደርያ) -ቢልዲጊሉ-አቡርሐሞ የሚወስደው መንገድ 28 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን ስድስት የገጠር ቀበሌዎችን ያገናኛል፡፡ በተመሳሳይ ከአቡርሐሞ – አበንዴ – ሸርቆሌ አፎንዴ የሚወስደው መንገድ 22 ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን ሶስት ቀበሌዎችን የሚያስተሳስር ነው፡፡
ፕሮግራሙ በምግብ ዋስትና (RCAP FOR FOOD SECURITY) ተቀርጾ በአለም ባንክ እና በክልሉ መንግስት የፋይናንስ ድጋፍ በአሶሳ ዞን አቡርሐሞ ወረዳ የሚገኙ ቀበሌዎችን በመሰረተ ልማት ለማገናኘት የጥገና ስራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ማህበረሰቡ የግብርና ምርቱን ወደ ገበያ በማውጣት እና ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥንም ዋነኛ ዓላማው አድርጓል፡፡
ከዚህ በመነሳትም የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ሁለቱ የመንገድ ስራዎች ጥገና ያሉበትን ሁኔታ ምልከታ አድርገዋል፡፡ ማህበረሰብንም አወያይተዋል፡፡ በቀጣይም ኮሚሽኑ በግንባታ ሂደት ባያቸው ክፍተቶች ላይ ለሚመለከታቸው አካላትና ባለድርሻዎች ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብና ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና ከአቡርሐሞ ወረዳ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የማህበረሰቡ የረጅም ጊዜ የመንገድ ጥያቄ በክልሉ መንግስት ምላሽ ማግኘቱ ተገልጧል፡፡ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅም ወረዳው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ እና መሰረተ ልማቱ በማህበረሱ እንዲጠበቅ እየተሰራ መሆኑን የአቡርሐሞ ወረዳ ም/አስተዳዳሪ ቄስ ደርቤ ተገኘ ተናግረዋል።
የጠጠር መንገድ ጥገናው በክልሉ መንግስት መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ባለቤትነት እየተካሄደ ሲሆን የክልሉ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን እንዲሰራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *