የመከታተያ ክፍሎችን ውጤታማነት ለማሳደግ ዞኑ በትከረት ይሰራል
አቶ ቢኒያም ጅሃድ
የመተከል ዞን መስተዳደር ተወከይና የዞኑ ሰላም ግንባታና ፀጥታ መመሪያ ኃላፊ
የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ የመተከል ዞን መስተዳደር በትኩረት እንደሚሰራ የመተከል ዞን መስተዳደር ተወከይና የዞኑ ሰላም ግንባታና ፀጥታ መመሪያ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ጅሃድ ተናገሩ፡፡
በግልገል በለስ ከተማ ለመከታተያ ክፍል ባለሙያዎች በተዘጋጀ የሥልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያሥተላለፉት አቶ ቢኒያም ጅሃድ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎች ደንብና መመሪያዎች እንዲጠበቁና የተሰጣቸውን የሥነ-ምግባር ግንባታ ሚና በአግባቡ እንዲወጡም ጥሪ አድርገዋል፡፡
በሥልጠናው ሙስናና ብልሹ አሰራርን መሸከም የማይችል፤ በኃላፊነትና በአገልጋይነት መንፈስ የሚሰራ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው እርብርብ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የአውታሮች አደረጃጀት ባለሙያ አቶ ሐብታሙ በዛብህ ተግባርና ኃለፊነት ጋር በተያያዘ ባቀረቡት ሰነድ አስረድተዋል፡፡
ሌላው የሐብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ስራ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ሂደት ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለፁት የኮሚሽኑ የሐብት ምዝገባና ማሳወቅ ባለሙያ አቶ አራጋው አሰፋ አመራሩና ባለሙያው የመንግስት ኃላፊነትና ስራን ከተቀበለበት ጊዜ ጀምሮ ሐብቱን ማስመዝገብ በሐብት ማስመዝገብና ማሳወቅ በአዋጅ ቁጥር 103/2004 እና ለአፈጻፃም እንዲረዳ በተሸሻለው መመሪያ ቁጥር 11/2014 መገለፁን አስታውሰዋል፡፡
ቅፆች በእውነተኛ መረጃና በጥራት ተሞልተው በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ወደ ኮሚሽኑ መላክ እንደሚገባም ባለሙያው አክለው አስገንዝበዋል፡፡
በሐብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ቅፅ ላይ ሐብታቸውን ለማስመዝገብ እምቢተኛ በሆኑ አካላት ላይም ደንብና መመሪያን ተከትሎ አስፈላጊው እንዲፈፀም ከሚመለከተው አካል ጋር በቅርበት መስራት እንደሚገባም አቶ አራጋው ተናግረዋል፡፡

