የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው፦ አቶ አሻድሊ ሀሰን

ወቅታዊ መረጃ

እንደሀገር የተጀመረው የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን አስታወቁ።

‎የኢፌዴሪ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ስርዓት (e-PG) ትግበራን በተመለከተ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰጥቷል።

‎የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ፣ ባለስልጣኑ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት የተጣጣመ የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳድር ስርዓት እንዲኖር እየሠራ ነው ብለዋል።

‎የግዥ ስርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ መሰረት፣ የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ወጪ ቆጣቢ፣ ግልጽና ቀልጣፋ የሚያደርግ  መሆኑን ተናግረዋል።

‎የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመስሪያ ቤቶች እና ለንግዱ ማህበረሰብ አስተዳድራዊ ወጪዎችን እንደሚቀንስ አንስተው፣ በአሁኑ ወቅት በስርዓቱን የሚጠቀሙ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች ቁጥር ወደ 262 ማደጉን አንስተዋል።

‎ኤሌክትሮኒክ የግዢ ስርዓትን በክልሎች ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ሁለቱን ከተማ አስተዳድሮች ጨምሮ 8 ክልሎች ወደ ሥርዓቱ የሚያስገቡ የዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።

‎የክልሉ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመተግበር በሚያደርገው ጥረት ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።

‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ መንግሥት በተቋማት ሪፎርም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በግዢ ስርዓቱ እየተደረገ ያለው ሪፎርም አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

‎የግዥ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

‎የክልሉ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመተግበር ቁርጠኛ ነው ያሉት አቶ አሻድሊ፣ ለዚሁ የሚያግዝ አዋጅ ተዘጋጅቶ መጽደቁን ገልጸዋል።

‎በክልሉ ወደ ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመግባት በሚደረገው ጥረት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጠቁመዋል።

 

 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *