
ኮሚሽኑ በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር፤ በጉባ ወረዳ ማንኩሽ ከተማ ያስገነባውን የመኖሪያ ቤት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪያ አቶ አህመድ ኩምሳሪ ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለወ/ሮ አሻ ባውር ቁልፉን አስረክቧል፡፡
ወ/ሮ አሻ ባውር ቁልፉን በተረከበቡት ወቅት እንዳሉት ስለተደረገላቸው ነገር ደስታቸውን ገልፀው፤ ለእሳቸው የተደረገው ድጋፍ ለሌሎችም እንዲደርስ አስተያዬታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የመኖሪያ ቤቱን ያስረከቡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ከማል ሃሰን መረዳዳትና፣ መተጋገዝ የአብሮነታችን መገለጫ ኢትዮጵያዊ እሴት በመሆኑ ኮሚሽኑ አበክሮ ይሰራበታል ነው ያሉት፡፡
ተቋሙ በተመሳሳይ በወረዳው ለሚኖሩ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ያዘጋጀውን ምግብ ነክ ድጋፍ አበርክቷል፡፡
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ኩምሳሪ በበኩላቸው የቤ/ጉ/ክ/መ/ሥነ-ምግባር ፀረሙስና ኮሚሽን በወረዳው ለሚኖሩ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ስላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ለማህበረሰባችን ያለንን ተቆርቋሪነት የሚያረጋግጥ፤ ወንድማማችነትንና አብሮነትን የሚጠናከር ተግባር በመሆኑ ይበልጥ ባህል ማድረግና ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
