የወርቅ ማዕድን ሐብት ስራ ሕጋዊ አሰራርን በመከተል ለሃገር ጥቅም እንዲውል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል – አቶ ቱጃኒ አደም (የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሃብት ቢሮ ኃላፊ)

ወቅታዊ መረጃ

በባምባሲ ወረዳ ከክልል፣ ዞንና ወረዳ የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች  በወረዳው  ከተሰማሩ የወርቅ አምራች ማህበራት ጋር ተወያይተዋል።

 

በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቱጃኒ አደም   በወረዳው የወርቅ ማዕድን ሃብት ስራ እየተስፋፋ መሆኑን አንስተው፤ ሃብቱን ለሃገር ጥቅም ለማዋል ሕጋዊ አሰራርን መከተልና ለውጤታማነቱም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም በተለይ በባምባሲ ወረዳ  በሺዎ ቀበሌ የወርቅ ማዕድን የማውጣት ስራ ለጊዜው  አሠራሩ የህግ ማዕቀፍ እስኪበጅለት   መታገዱን ገልፀዋል፡፡

 

የባምባሲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልዋሂድ አዙቤር በበኩላቸው የወረዳውን የማዕድን ሃብቶች በአግባቡ ለማልማት  ህገ-ወጥ የወርቅ ስራን የሚከላከል ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

 

በተየያዘ ዜና  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ም/ ኃላፊ አቶ ኦሳም ዩሱፍ የወርቅ ማዕድን ሃብት  የአካባቢን ሥነ-ምህዳር በጠበቀና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ  ቴክኖሎጅዎችንና ዘመናዊ አስራሮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ  ጠቁመዋል፡፡ መሰል በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረምም  ውይይት የጎላ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

 

በዚህ መድረክ  የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳድር አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም  የወርቅ አምራቾች ተሳትፈዋል ፡፡

 

ከባምባሲ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ለገጻችን እንዲያመች ተደርጎ የተወሰደ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *