
(አሶሳ፣ኅዳር 18/2018 ዓ/ም) የቤጉ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ማድረጉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የማዕከሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ።
የቤጉ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ቦርድ የማዕከሉን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ እና የማዕከሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን አብዲሳ ፤ በክልሉ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ቤጉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከተቋቋመ ወዲህ የዜጎችን እንግልት በማስቀረት ግልጸኝነትንና ተጠያቂነት እንዲፈጠር እያገዘ እንደሆነ አቶ ጌታሁን ገልጸዋል።
ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮች እርካታን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ማዕከል እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
የቤጉ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰመረ ጅራታ (ኢ/ር)፣ ማዕከሉ እስካሁን ድረስ ከ3 ሺህ በላይ ለሚልቁ ዜጎች በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል ተበታትነው አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ተቋማትን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቤጉ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና በኢፌዴሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ጳጉሜ 5/2017 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል።
ዘገባው የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው፤
