በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ መገንባት የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል –  ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ

ወቅታዊ መረጃ

 

 

‎(አሶሳ፣ ኅዳር 26/2018 ዓ/ም) ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ ገለጹ።

‎በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል በዓለማቀፍ ደረጃ 22ኛው፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 21ኛው የጸረ-ሙስና ቀን በክልል ደረጃ ዛሬ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ‎ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ፣ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ መገንባት ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል።

‎ለዚህም ትውልዱን ከታች ጀምሮ በስነ-ምግባር ማነጽ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ተናግረዋል።

‎የመንግሥት ተቋማት ተጋልጋዮችን ከማጉላላት እና ከእጅ መንሻ የጸዳ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር ዘርግተው ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

‎በኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ውስጥ ሙስናን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ከመጸየፍ ባለፈ ተግባሩን ማጋለጥ እና ተገቢ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ወ/ሮ አስካለች ገልጸዋል።

‎የክልሉ ስነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ከማል ሀሰን፣ ሙስና በዓለማቀፍ ደረጃ ልማት እና ብልጽግና እንዳይረጋገጥ ቀደሚ ስጋት መሆኑን አንስተዋል።

‎ሙስናና ብልሹ አሰራር የሚፈጸምበት መንገድ ውስብስብ እና ድብቅ በመሆኑ በአንድ ተቋም ብቻ ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በጸረ-ሙስና ትግል ውስጥ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

‎የጸረ-ሙስና ቀንን ከማክበር ባለፈ ትውልድን በስነ-ምግባር ለማነጽ እና የተቋማትን አገልግሎት በማሻሻል ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

‎#የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *