ሙስናና ብልሹ አሰራርን በቅንጅት መታግል የሚያስችል የፍትህ አካላት ግምገማዊ ስልጠና ተካሄደ፡፡
******************
የሙስና ወንጀልን መከላከል፣ መክሰስና መመርመር የሚችሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ጠ.ዐቃቤ ህግ እና የፖሊስ ኮሚሽን ተቋማት በቅንጅት አለመስራት ለፀረ-ሙስና ትግሉ ክፍተት መፍጠሩ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡
በዚህ ሃሳብ መነሻነት ከላይ የተገለፁት ሶስቱ የፍትህ አካት የሙስና ወንጀሎችን መከላከል መክሰስና መመርመር የሚያስችል ሰፊ ውይይት በአሶሳ ከተማ አድርገዋል፡፡
መድረኩን የከፈቱት ኮሚሽር መንግስቱ ላሎ የግምገማዊ ስልጠናው ዋና አላማ የሙስና ወንጀሎችን የመከላከል፣ የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ስራውን በቅንጅት፣ በትብበርና በመናበብ በመስራት በተለያዩ ዘርፎች ህዝብን እያስለቀሰ የሚገኘውን የሙስና ወንጀልና ሙሰኞችን አደብ ማስገዛት መሆኑን አውስተዋል፡፡
በግምገማዊ ስልጠናው ተለምዷዊ አሰራር፣ የአደረጃጀት ችግር፣ የዕውቀትና የክህሎት ክፍተቶች፣ የጥቆማ አቀባበል የተቀላጠፈና አንድ ቋት አለመሆን፣ የሙስና ወንጀሎችን መለየት አለመቻል፣ የምርመራ ስራዎች ሚስጢር አለመጠበቅ፣ የክስ አቀራረብና የውሳኔ አሰጣጥ መዛነፍ ሌብነትን ለመታገል ፈታና መሆናቸው ተገልጧል፡፡
ችግሮችን ለመፍታትም በአደረጃጀት የሚፈቱትን ለማስተካከል በቅንጅት እንደሚሰራ፤ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው አካለት እና ባለሙያዎችም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡ ይህ ካልሆነ መንግስት በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን እስከማሰናበት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አየሁ አሳስበዋል፡፡
በግምገማዊ ሥልጠናው የሙስና ፅንሰ ሃሳብና የሙስና ወንጀሎችና የሥነ-ስርዓት ህጉን የሚመለከቱ ይዘቶች በአቶ ገዛኸኝ የኔው (የሥልጠና ኬዝ ቲም ቡድን መሪ) እና አቶ ይታገሱ አላማው (ዐቃቤ ህግ) እንደቅደምተከተላቸው ቀርበው ሰፊ ግንዛቤ ተይዞበታል፡፡
በማጠቃለያው ስልጣንና ኃላፊነት ያለቸው አካለት እያሉ በዚህ ልክ የሙስና መንሰራፋት አስደንጋጭ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ማህበረሰቡ በሙሰኞችና ሌቦች እየደረሰበት ላለው ችግር መፍትሄ ለመስጠት የዘርፉ ባለሙያዎች እራሳቸውን እንዲፈትሹና ተቋማቱ በተቀናጀ ሁኔታ መስራት የሚያስችላቸውን ቀጣይነት ያለው የግንኙነትና የትብብር መስመር መቀየስ እንደሚገባቸው ተመላክቷል፡፡
