በትራንስፓርት እና በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋለው የተጋነነ ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ መባባሱን ቀጥሏል፡፡ ለማህበረሰቡም ኑሮን ለመግፋት ትልቁ ፈተና ሁኖ ዘልቋል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም መንግስት ከማህበረሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በየደረጃው የሚገኘው አመራር የኑሮ ጫናውን ሊያቀሉ የሚችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
በቅርቡም የፍትህ አካላትን፣ በትራንስስፖርትና በንግዱ ዘርፍ የሚሰሩ ኃላፊዎችና አመራሮችን የያዘ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
ግብረ ኃይሉ በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ በመሰብሰብ በ100 ቀናት መፍትሄ ለመስጠት ያሰችለኛል ያለውን ጥልቅ ውይይት አድርጓል፡፡
በዋናነትም በንግዱ ዘርፍ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ የሚደረግ ጤናማ ያልሆነ ውድድር፣ በግጭትና በሰላም የለም ሰበብ የመበልፀግ ፍላጎቶች በነጋዴው ዘንድ መስተዋል፣ ያለደረሰኝ መሸጥ እና ከተመን በላይ መግዛት ለቁጥጥርና ለክትትል አስቸጋሪ መሆን ፣ አንዳንድ የፍትህ አካላት ጭምር የኑሮ ውድነቱን ሊያባብሱ በሚችሉ ህገ ወጥ ስራዎች መሳተፍ ለችግሩ መባባስ ቁንጮ ምክንያቶች መሆናቸው ተንፀባርቋል፡፡
የኑሮ ውድነቱ የራሱ የሆነ አለም አቀፍና አገር አቀፍ አመክንዬ ቢኖረውም የተጋነነ እና በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶች ጭምር ዋጋቸው እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ግብረ- ኃይሉ እስከ አሁን አበረታች ስራዎች መስራቱ ተመላክቷል፡፡ ነገር ግን አሁንም በርካታ የቤት ስራዎች እንደሚቀሩት በተሳታፊዎች ተጠቁሟል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም በመሰል ህገ ወጥ ድርጊቶች የሚሳተፉ አካለት ላይ ንግድ ፍቃዳቸውን ከመሰረዝ ጀምሮ በህግ አግባብ ተጠያቂ የሚሆኑበትና ፍርድ ቤቶችም ለዚሁ ስራ ዝግጁ በሚሆኑበት ደረጃ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
ግብረ ኃይሉ በኑሮ ውድነት ለሚሰቃየው ማህበረሰብ በአጭር ጊዜ የእፎይታ መፍትሄ እንደሚያመጣ ታምኖበታል፡፡
