(አሶሳ፤ ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም) የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ድፍረት የተሞላበትና የማያቋርጥ የፀረ-ሙስና ትግል ማድረግ እንደሚገባቸው ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ አሳሰቡ፡፡
የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ሙስናን በመከላከል ረገድ ባሳለፍነው የበጀት አመት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና አመራሮች የመከታተያ ክፍሎችን እንደ አንድ የሥራ አጋር መቁጠር መጀመራቸውና በመመካከር ስራ ለመስራት የሚያደርጉት ጥረትም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ ይህን ያሉት ለሶስት ቀናት በዕቅድ መናበብና በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ዙሪያ ሲደረግ በነበር የማጠቃለያ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
በመድረኩ ከመከታተያ ክፍሎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ማብራሪያና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ የሰጡት ኮሚሽነር መንግስቱ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎች በግብረ ገብና በታታሪነት አርዓያ የሚሆኑ፤ ከግል ጥቅም ይልቅ የተቋምና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያስበልጡ፤ ከፀረ-ሌብነት ትግሉ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በፅናት የሚታገሉ፤ የአሰራር ጥናት፣ የሐብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ስራ በመስራት እንዲሁም የሥነ-ምግባርና የሞራል እሴቶች ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት የሕዝብና የመንግስትን ሃብትና ንብረት ከመመዝበሩ በፊት የቅድመ-መከላከል ስራዎችን ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስረግጠዋል፡፡
በዚህ መድረክ ለፀረ-ሙስና ትግሉ የሚያግዛቸውን በቂ እውቀትና ልምድ ያገኙ መሆኑን የገለፁት ተሳታፊዎች መሰል መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

You, Mengistu Lalo, Sinshaw Shitu Msadv and 32 others
