1ኛ. ተከሳሽ አቶ ኢታና ለታ ጉርሜሳ፣
2ኛ. ተከሳሽ አቶ ተካልኝ አብነው አርሳ፣
3ኛ. ተከሳሽ አቶ ታርጃት ካት ራት
ተከሳሾች መንግስትና ህዝብን በታማኝነት እንዲያገለግሉ በኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅን አሶሳ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ያገኙትን የሥራ እድል ተገቢ ያልሆነ ብልፅግናን ለማግኘት ተጠቅመውበታል፤ ይላል ከሳሽ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት፡፡
1ኛ. ተከሳሽ አቶ ኢታና ለታ ጉርሜሳ የሪጅኑ ፋይናንስ ክፍል ካሸሪ በመሆን ሲያገለግል በተቋሙ የባንክ አካውንት ማስገባት ይገባው የነበረን በየእለቱ የሰበሰበውን ብር 531, 650. 17፣ ከ2ኛ ተከሳሽ በሞባይል ሒሳብ ቁጥር የተላለፈለትን ብር 840, 050፣ ከ3ኛ ተከሳሽ የተላለፈለትን ብር 483, 000፤ በአጠቃላይ በስራ አጋጣሚ በእጁ የገባውን ብር 1 ሚሊዬን 847 ሽህ ከ17 ሳንቲም ለግል ጥቅም በማዋል በተቋሙ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል፡፡
2ኛ እና 3ተኛ ተከሳሽ የተቋሙ የሽያጭ ሰራተኛ ሁነው ሲያገለግሉ በገንዘብ አሰባሰብ መመሪያ መሰረት ደንበኞች የሚከፍሉትን ማንኛውም ክፍያ ለካሸሪ ማስረከብና የሲስተም ደረሰኝ መቀበል ሲጠበቅባቸው ይህን ባለማድረጋቸው የተቋሙ ገንዘብ እንዲመዘበር በማድረግ በተቋሙ ሃብት ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተዋናይ ሁነዋል፡፡
የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሲያደራጅ የቆየው የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬትም በወንጀሉ ላይ እንደነበራቸው ሚና፤ 1ኛ ተከሳሽን በከባድ የእምነት ማጉደል፣ 2ኛ ተከሳሽን የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን መምራት የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቧባቸዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳና አካባቢው 1ኛ ተዘዋዋሪ ችሎት በወንጀል ህግ አንቀፅ ቁጥር 32/1ሀ/ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ ቁጥር 3 እና 31/2/ የተደነገገውን በመተላለፍ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳና አካባቢው 1ኛ ተዘዋዋሪ ችሎት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ኢታና ለታ ጉርሜሳ በ 8 አመት ከ 5 ወር ፅኑ እስራትና በ 7,000 ብር የገንዘብ መቀጮ፤ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ተካልኝ አብነው አርሳ በ 4 ዓመት ከ 6 ወር ፅኑ እስራትና 2, 000 ብር የገንዘብ መቀጮ ፣ 3ኛ ተከሳሽ አቶ ታርጃት ካት ራት በ 6 ወር ቀላል እስርና በ 1,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሶሳና አካባቢው 1ኛ ተዘዋዋሪ ችሎት ብይን ሰጥቷል፡፡
