22ኛው አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የታለመለትን ግብ እንዲመታ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉአመራሮች፤ በተለይም በመስሪያ ቤቶች ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያዎችን በማገዝ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የኮሚሽኑ የሙስና ወንጀሎችና ብልሹ አሰራር መከላከል ዳይሬክተር አቶ ጊሳ ዚፍሃ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት ዛሬ በአሶሳ ከተማ የክልሉ መስተዳድር ቅጥር ግቢ በክልል መስሪያ ቤቶች እና በአሶሳ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ተቋማት ከሚሰሩ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙዎች ጋር በተደረገ ውይይት ነው፡፡ እለቱን ለማክበር በሚሰሩ ዋና ዋና ተግባራት እና ግልፅነት በሚሹ ጉዳዮች ላይም ዳይሬክተሩ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
የበዓሉ ማስፈፀሚያ እቅድ እና አስፈላጊ ግብዓቶችም በተቋሙ የአውታሮች አደረጃጀት ቡድን መሪ ወ/ሮ መሰረት ግርማይ በኩል ቀርቧል፡፡
በዓሉን የማክበር አላማ፤ ታሪካዊውን የፀረ-ሙስና ትግል፤ ዓለም አቀፍ ትብብርና የቃል ኪዳን ቀን ከማስታወስ ባሻገር፤ ሰፋፊ የፀረ-ሙስና ንቅናቄዎችን ማካሄድ፣ ለፀረ-ሙስና ትግሉ የታደሰ ቁመና መፍጠር፣ ሁሉን አቀፍ ትብብር፣ ትስስርና ቅንጅትን ማረጋገጥ ሲሆን፤ መሪ ቃሉም “ትውልድን በሥነ-ምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!” የሚል መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

