አቶ ሲሳይ ጌታነህ (በባምባሲ ወረዳ የአስተዳደር ዘርፍ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ባለሙያ) ሙስናና ብልሹ አሰራር ዛሬ ላይ ድርሻው ይለያይ እንጅ በየትኛውም ዘርፍ ላይ እንደሚስተዋል በስራቸው መታዘባቸውን ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን በትምህርቱ ዘርፍና እና በሰራተኛ ቅጥር፣ ዝውውር ተያያዥ ጉዳዮች የሚፈፀመው ሌብነት አይን ያወጣና የሚያደርሰው ጉዳትም እንደሳቸው ገለፃ የከፋ ነው፡፡
የትምህርቱ ዘርፍ የማህበረሰብን አስተሳሰብ በላቀ እውቀት በመገንባት የተሻለ ሃገርና ህዝብ ለመፍጠር የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ዘርፉን የጥቅም ማጋበሻ ዋነኛ ምንጭ ያደረጉ ግለሰቦች እና አካላት በዘርፉ ሃገርና ትውልድ እንዳይጠቀም እውቀትን የሚሻ ትውልድ እንዳይፈጠር አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡
በዚሁ ዘርፍ የዕድሜያቸውን ግማሽ ጨርሰው ዲፕሎማ፣ ዲግሪ እና ማስተርስ ይዘው የሚመረቁ ተማሪዎች በቅጥር፣ ዝውውር እና የደረጃ እድገት ከደንብና መመሪያ ውጭ በሚፈፀም አሰራር የሌቦች ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያው ገለፃ ከሆነ ከደንብና መመሪያ ውጭ የሚቀጠሩ ባለሙያዎች አንድም ለቦታው የሚመጥን አቅም የሌላቸው በሌላ በኩል ቦታው የሚፈልገውን የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ የማያሟሉ ናቸው፡፡ ይህም ለመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮች በር የሚከፍት ነው፡፡
በሌላ በኩል ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የትምህርቱንና የሙህራን ዋጋ እያሳጣ ይጋኛል፡፡ በስውር ከሚሰሩ የትምህርት ማስረጃዎች በተጨማሪ በኮሌጆች የሚሰጡ የትምህርት ማስረጃዎች ተማሪዎች በትክክል ተምረው ስለማግኘታቸው በስራ ገበታቸው ያላቸው ብቃት ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
በአገልግሎቱ ዘርፈ ለሚስተዋል ብልሹ አሰራር ዋነኛ ምክንያትም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ይገልፃሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የሚፈጠሩ ብልሹ አሰራሮች የኋላ ኋላ ማህበረሰብን ለእንግልትና ለምሬት ዳርጎ መንግስት በህዝብ አመኔታ እንዲያጣ ይዳርጋሉ፡፡
ሙስናና ብልሹ አሰራር የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነሰም ማህበረሰቡ በእጅ መንሻ አገልግሎትን ከመግዛት ታቅቦ ደንብና መመሪያዎች እንዲፈፀሙ መታገል፡፡ ሙስና ተፈጽሟል ብለው ሲያስቡም ከተራ አሉባልታና ስሜታዊነት በመውጣት በመረጃና በማስረጃ እስከመጨረሻው ሌቦችን በመታገል በየደረጃው የሚገኙ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎችን ማገዝ፤ የፍትህ አካላትም በተለያዩ ዘርፎች ሙስናና ብልሹ አሰራር በሚፈፅሙ አካላት እየወሰዱ ያሉትን እርምጃ አጠናክረው መቀጠልና ሌቦችን አደብ በማስገዛት የማህበረሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡

You, Mengistu Lalo, Yilma Tilahun and 30 others
